የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅት በካፒታል ገበያው ውስጥ የሚኖረው ሚና እና ኃላፊነት ምንድነው ?
የካፒታል ገበያ – መረጃ ፣ ዕውቀትና ዕምነት የሚፈልግ ገበያ ነው ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅት በካፒታል ገበያው ውስጥ የሚኖረውን ሚና እና ኃላፊነት እንመለከታለን፡፡
ትክክለኛ ዋጋ መኖሩን ማረጋገጥ !
የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅቶች እንደ አክሲዮኖችና ቦንዶች ያሉ የኢንቨስትመንት ንብረቶችን ትክክለኛ የገበያ ዋጋ ይገምታሉ። ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ መግለጫዎችን፣ የገበያ ሁኔታዎችንና ስጋቶችን የመተንተንን፡ የፖርትፎሊዮ ዋጋ የመገመት፡ የውህደትና ግዢ ሂደት ላይ የግምት ስራ ማከናወንን ይጨምራል ። በዚህ ሂደት ውስጥ ትክክለኛ ግምቶችን በማቅረብ ባለሀብቶች በመረጃ ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ውሳኔ እንዲያደርጉ እና የኢንቨስትመንት አደጋን እንዲመዝኑ ይረዳሉ።
የገበያ ግልፅነትን ማምጣት !
ፍትሃዊ የሰነድ ግምቶች በካፒታል ገበያ ውስጥ ግልጽነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ባለሀብቶች አንድን የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ዋጋ አሁን ካለው የገበያ ዋጋ ጋር በማነፃፀር እምቅ እድሎችን ወይም ከልክ በላይ የተገመቱ ሰነዶችን መለየት ይችላሉ። ይህ ግልጽነት በመጨረሻ በገበያው ውስጥ መተማመንን ይፈጥራል።
የፋይናንስ መረጋጋትን መፍጠር !
የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓትን ለመጠበቅ የኢንቨስትመንት ሰነዶች ትክክለኛ ግምት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመጠን በላይ የተጋነኑ ዋጋዎች በገበያው ውስጥ መኖር የገበያ ውድቀት ያስከትላል፡፡ አስተማማኝ የሰነድ ግምት አገልግሎት በመስጠት፡ የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅቶች የፋይናንስ አለመረጋጋትን መከላከልና የካፒታል ገበያን የረዥም ጊዜ ጤናማ ሂደት ለማረጋገጥ ይረዳሉ።
በኢትዮጲያ የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን ዕውቅና አግኝቶ ወደስራ የሚገባ ማንኛውም የሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገማች ድርጅት እነዚህ ከላይ የተገለፁ ሚናዎችና ኃላፊነቶች እንዳሉበት በመመሪያው ላይ በግልፅ ተመላክቶ ይገኛል፡፡
